የ1447ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በታላቅ ድምቀት ተከበረ።
መጋቢት 11/2018| የዘንድሮው የ1447ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል በማዕከሉ ውስጥ ከሚገኙ ሰልጣኞች፣ አሰልጣኞች እና ሰራተኞች ጋር በጋራ በመሆን በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የማዕከሉ ስራ አስፈፃሚዎች ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ረመዳን የሰላም፣ የፍቅር እና የመረዳዳት ወር እንደመሆኑ መጠን በማዕከሉ ውስጥ ያለው ወንድማማችነት እና አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም በዓሉን አስመልክተው የማዕከሉ ዋና ዲን አቶ ሙሀመድ ጃርሶ መልዕክት አስተላልፈዋል የረመዳን ፆም ወር የራስን ስነ-ምግባር የምንገነባበት ትዕግስትን የምንለማመድበትና አቅመ ደካሞችን የምንረዳበት ታላቅ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት መሆኑና ዛሬ የምናከብረው የዒድ አል-ፈጥር በዓልም ይህንን የተቀደሰ እሴት በተግባር የምናሳይበትና አብሮነታችንን የምናጠናክርበት ዕለትም ነው ብለዋል።
አክለውም ዋና ዲኑ በማዕከሉ ውስጥ የሚታየው የሃይማኖት እና የባህል ብዝሃነት ለተቋሙ ጥንካሬ መሆኑን ጠቅሰው ሰልጣኞች በፆሙ ወቅት ያሳዩትን ታላቅ ዲሲፕሊን እና ትጋት ወደ ስፖርታዊ ስልጠናቸው በማምጣት ለሀገር ኩራት የሚሆን ውጤት እንዲያስመዘግቡ አሳስበዋል።

