የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የ2018 የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ባለድል በመሆን ዋንጫውን ተረከበ

ሚያዚያ 28/2018| የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የ2018 የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ የውድድር ዘመንን በድል በማጠናቀቅ የሻምፒዮናነት ዋንጫ በልበ ሙሉነት አንስቷል።
ቡድኑ ዋንጫውን ማግኘቱን ቀድሞ አረጋግጦ ወደ ሜዳ ቢገባም በመዝጊያ ጨዋታው ላይ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጋር ባደረገው እጅግ ጠንካራ የሆነ ጨዋታ 4 ለ 3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የድል በዓሉን አድምቆታል። በተለይም ማዕከሉ በሊጉ ሁለተኛ ዙር የጨዋታ መርሃ ግብር ላይ ምንም አይነት ሽንፈት ሳያስተናግድ ሊጉን በበላይነት ማጠናቀቁ የክለቡን ጥንካሬና የቴክኒክ ብቃት በግልጽ ያሳየ ሆኗል።
በሊጉ መዝጊያ እና የዋንጫ ሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስፖርት አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን አቶ ኢሳያስ ጂራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የፊፋ ፀረ-ዘረኝነትና ፀረ-አግላይነት ኮሚቴ አባል፤ አቶ ደሳለኝ በላይ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የትምህርትና ስልጠና ምክትል ዋና ዳይሬክተር፤ አቶ መሃመድ ጃርሶ የማዕከሉ ዋና ዲን እንዲሁም የማዕከሉ ማኔጅመንት አባላትና አሰልጣኞች በክብር ተገኝተው ለባለድሎቹ እውቅና ሰጥተዋል።
የማዕከሉ ስኬት በቡድን ውጤት ብቻ ሳይወሰን በግል ብቃትም የታጀበ የሆነ ሲሆን በውድድሩ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ልዲያ ኢያሱ በደመቀ ሁኔታ አጠናቃለች። ልዲያ በመዝጊያው ጨዋታ ላይ ሁለት ወሳኝ ግቦችን በማስቆጠር በአጠቃላይ በውድድር ዘመኑ 19 ግቦችን በማስመዝገብ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብርን ተቀናጅታለች።
ለዚህ ታሪካዊ ስኬት መገኘት የአሰልጣኙ ሚና ከፍተኛ ሲሆን ቡድኑን በስነ-ልቦና እና በታክቲክ በመቅረጽ በተለይም በሁለተኛው ዙር ያለ ምንም ሽንፈት ለዋንጫ እንዲበቃ ላደረጉት #አሰልጣኝ_ሰለሞን_ገለታ ልዩ አድናቆት ቀርቧል። አሰልጣኙ ካላቸው ልምድና ለስፖርተኞቹ ካላቸው ቅርበት አንጻር ቡድኑ ወጥ የሆነ አቋም እንዲኖረውና ውጤታማ እንዲሆን ያስቻለ ስራ መስራታቸው በመዝጊያ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
ድሉን በድል አክሎ ዋንጫውን የጨበጠው የልዑካን ቡድኑ አሰላ በሚገኘው የማዕከሉ ዋና ግቢ ሲደርስ በማዕከሉ ማህበረሰብ እና በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ ደማቅና እጅግ አበረታች አቀባበል ተደርጎለታል። ይህ ውጤት ማዕከሉ በሴቶች እግር ኳስ እያሳየ የመጣውን እድገትና ለሀገሪቱ ስፖርት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ዳግም ያረጋገጠ ሆኖ ተመዝግቧል።
በመጨረሻም የማዕከሉ ዋና ዲን አቶ መሃመድ ጃርሶ ለቡድኑ ስኬት መሰረት የሆኑትን አሰልጣኝ ሰለሞን ገለታን አመስግነዋል። አሰልጣኙ ካላቸው ከፍተኛ የቴክኒክ ብቃትና ለስፖርተኞቹ ከሚሰጡት አባታዊ ምክር ባሻገር ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ያለ ምንም ሽንፈት ለዋንጫ እንዲበቃ ላደረጉት ተከታታይ ጥረትና ላሳዩት ቁርጠኝነት ማዕከሉ ያለውን ጥልቅ አድናቆት ገልጸዋል።
ሳይንሳዊ ስልጠና ቀጣይነት ላላው ተተኪ አትሌቶች “
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://atdatc.edu.et

Email: info@atdatc.edu.et

See less

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *